02/02/2026
ፆመ ነነዌ ቤተክርስቲያናችን ካወጀቻቸው ሰባቱ አፃማት ውስጥ አንዷ ነች ነነዌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታሪካቸው በስፋት ከተጻፈላቸው የሜሶፖታምያ ከተሞች አንዷ ናት፡፡
ብዙ የሥነ መለኲት ምሁራን ከዛሬዋ የሞሱል ከተማ በተቃራኒ ከባግዳድ ሰሜን ምዕራብ 350 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ እንደ ነበረች ይስማማሉ፡፡
በዚህች ከተማ የሚኖሩት ሰዎች የሚሠሩት ክፋትና ኃጢአት እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ ጽዋው ሞልቶ መጥፊያቸው ስለ ደረሰ ለፍጥረቱ ርኅራኄ ያለው እግዚአብሔር ግን ንስሐ ይገቡ ዘንድ ነብዩ ዮናስን ልኮላቸዋል፡፡
ይህ ነብይ ከአሕዛብ ወደ አሕዛብ የተላከ ነብይ ነው፡፡ አላላኩም አንድ ነብይ ወደ እስራኤላውያን ተልኮ እንደሚያደርገው ለመገሰጽ ሳይሆን ወደ ንስሐ ይጠራቸው ዘንድ ነበር፡፡
ነገር ግን ነብዩ ወደዚያች ከተማ እንዲሄድ በእግዚአብሔር ቢታዘዝም ወደ ተርሴስ ሲኮበልል እንመለከተዋለን፡፡
ቅዱስ ጄሮም ነብዩ ለምን እንዲህ እንዳደረገ ሲናገር፡- “ዮናስ አሕዛብን ከመጥላቱ የተነሣ ሳይሆን መዳን ከእስራኤል እየራቀ መሆኑን በትንቢት መነጽር ሲመለከት ወደ ነነዌ አልሄድም አለ፡፡
ይኸውም ሙሴ ይህን ሕዝብ ከምታጠፋው እኔን ከሕይወት መጽሐፍህ ደምስሰኝ ያለው ዓይነት ነበር 《ዘጸ.32፡31-32》፡፡
ቅዱስ ጳውሎስም “ስለ እነርሱ እርሱ ቢረገም እንደሚመርጥ እንደሰማነው” ብሏል 《ሮሜ.9፡3》፡፡
በእርግጥም በዘመነ ሐዲስ አሕዛብ በክርስቶስ አምነው ሲጠመቁ እስራኤል ግን መጻሕፍትን ብቻ ይዘው ቀርተዋል፤ እስራኤል ነብያትን ብቻ ይዘው ሲቀሩ አሕዛብ ግን የነብያቱን የትንቢት ፍጻሜ ይዘዋል 《ማቴ.12፡42》፡፡
ልብና ኩላሊት ያመላለሰውን የሚያውቅ አምላክ ግን ዮናስ ላለመታዘዝ ብሎ እንዳላደረገው ስላወቀ በልዩ ጥበቡ ሲወስደው እናያለን፡፡
አስቀድሞ ታላቅ ነፋስን በመርከቢቱ ላይ አመጣ፤ ዮናስን የሚውጥ ታላቅ ዓሣ አሰናዳ፤ ቀጥሎም ዓሣው በየብስ እንዲተፋው አደረገ፡፡
ዮናስ ወደዚያች ከተማ ከደረሰ በኋላ ግን ምንም እንኳን የሦስት ቀን መንገድ ዙሮ መስበክ ቢጠበቅበትም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሊገባ ጀመረ፤ ጮኾም በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች አለ።
የነነዌም ሰዎች #እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ። ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ። አዋጅም አስነገረ፥ በነነዌም ውስጥ የንጉሡንና የመኳንንቱን ትእዛዝ አሳወጀ፥ እንዲህም አለ፡- “ሰዎችና እንስሶች ላሞችና በጎች አንዳችን አይቅመሱ፤ አይሰማሩም ውኃንም አይጠጡ፤ ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፥ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ይጩኹ፤ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ።
እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደ ሆነ፥ ከጽኑ ቍጣውም ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?” ሰው ወዳጁ ጌታም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ፤ ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም።
አሁን ላይም እነደነነዌ ሰዎች ክፋት ሀጢያታችን በዝቶ የመጣ ትልቅ መከራ ና ችግር ደርሶብናል እና አባቶች እንዳዘዙን እንደነነዌ ህዝብ ማቅ ለብሰን ፆም ፀሎታችንን ከሰኞ 25_27ድረስ እናቀርባለን !!
የጭንቅ አማላጇ ልጅሽን ለምኚልን አሜን፫🙏