05/09/2025
"እምርታ ለዘላቂ ከፍታ" በሚል መሪ ቃል ታላቅ የንግድ ኤግዚብሽንና ባዛር ተከፈተ።
ነሀሴ 30/2017 ዓ.ም
አራዳ ወረዳ 5 ኮሙኒኬሽን
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ፒያሳ አካባቢ "እምርታ ለዘላቂ ከፍታ" በሚል መሪ ቃል በተከፈተው ታላቅ የንግድ ኤግዚብሽንና ባዛር ላይ ወ/ሮ ሽታየ መሀመድ የአዲስ አበባ ከተማ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ አቶ መስፍን አሰፋ የአዲስ አበባ ንግድ ድርጅት ሀላፊን ጨምሮ የከተማ ፣ የክ/ከተማና የወረዳ አመራሮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ በመክፈቻ ዝግጅቱ ላይ እንደተናገሩት በአሉን ያለምንም ችግር ለማክበርና ዘላቂ የተረጋጋ የግብይት ስርአት እንዲኖር የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው በዛሬው እለት እስከ ጳጉሜ 5/2017 ዓ.ም የሚቆዩ በከተማ ደረጃ 20 ታላላቅ ባዛሮች መከፈታቸውንና ቀደም ሲል አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ከ219 በላይ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በታላቅ ቅናሽ አገልግሎት የሚሰጡ በመሆኑ ህብረተሰቡ ተረጋግቶ ግብይት እንዲፈጽም መልእክት አስተላልፈዋል።
ወ/ሮ ሀቢባ አክለውም የዋጋ ጭማሪ ሲያጋጥም ነዋሪው በአቅራቢያው ለሚገኙ ንግድ ጽ/ቤቶች ጥቆማ በመስጠት አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪን በመከላከል ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አሳስበዋል።
የአራዳ ክ/ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌታሁን አበራ በበኩላቸው በባዛሩ ላይ ለበአሉ ግብአት የሚሆኑ የግብርና ምርቶች፣ የእንስሳት ተዋጽኦ፣ የኢንዱስትሪ ምርቶችና አልባሳት በብዛትና በጥራት መቅረባቸውን ገልጸው ፍትሃዊ ግብይት እንዲኖር አስተዳደሩ ባዛሮችን በማዘጋጀትና የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን በማጠናከር በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።