የኛ ነገር Yegna Neger.

የኛ ነገር Yegna Neger. ትዝታ ለሕይወት ሥር ሲሆን፣
ተስፋ ደግሞ ወደፊት የሚያራምደን ኃይል ነው።

12/06/2026

የተከፈተ በር

የቤታችን በሩ ፤
ከፍተሽው እንደሄድሽ ፤ዛሬም አልተዘጋም
የነበረኝ የለም፤ ለቀማኛ አልሰጋም

እምቢ ካልሽ እምቢ ነው ፤ፅኑ ነው ያንች ቃል
እንደማትመለሽ ፤አእምሮየ ያውቃል

ግን አልፈርድበትም፤ልቤ ቢያመነታ
ምኞት በሞላው ቤት ፤እውቀት የለው ቦታ

ተስፋ አይቆርጥም ደሞ፤
ልቤ ህልሙን ያምናል
ይለኛል ደጋግሞ፤
“ትመለስ ይሆናል
ትመለስ ይሆናል
ትመለስ ይሆናል፤”

እኔም በምላሹ ፤ ልቤን ፊት ሳልሰጠው
እንዲህ እለዋለሁ፤ ተስፋ ላስቆርጠው

“ጠጠር ላይቀቀል፤ አልማዝ ላይከለስ
በደመና ራስጌ፤ ጎጆ ላይቀለስ
እኔም አልሻሻል፤ እሱዋም አትመለስ፤

ሰማይ ሰም ይመስል፤ ቢንጠባጠብ ቀልጦ
የረር ፈልሶ ቢሸሽ፤ ቢከተል እንጦጦ
ባህሮች ቢከስሙ፤ ምድር ብትናወጥ
እሱዋም አትመለስ ፤እኔም አልለወጥ”

በዙርያየ ያለው ፀጋ ብዙ ነበር፤
ግና ክንፍ አብቅሎ
ፍቅርሽ ጥሎኝ ሲበር
ከኔ ጋር የቀረው
የተቆለፈ ልብ፤ የተከፈተ በር፡፡

በውቀቱ ስዩም

12/06/2026

"እብድ ጊዜ"

ዛሬ ቀጥረሽኝ ዛሬ ድረሽ፣
ከዛሬም አሁን፣ ከአሁንም ቀድመሽ፤
"እንግዲህ እመጣለሁ" ብለሽ፣
ካጓጓሽኝ ወዲህ ጊዜውን ቅደሚው።

ተፈጥሮን እምቢ በይ፣
እንደ አዛብ ቀጠሮ "ዛሬ ነገ" አትበይ፤
ብትችይ ግን፣
ትላንት ነይ!

— ሐብታሙ ሐድራ,

12/06/2026

ሐሳብ እንደ ሙክት፣
በቃል እያሰባን፤
የድንገት የገሃድ
ጥላሸት እየቀባን።

ለታከቱት ሁሉ፣
ከአንጀት እያነባን፤
ልክ እንደ ኩይሳ፣
ምስጥ እንዳይገነባን።

መገፋት ገፍቶን ነው፣
ሱባኤ የገባን።

በሰለሞን ሰሐለ✍️

12/06/2026

መቅደላ አፋፍ ላይ፣
ጩኸት ተበረከተ፤
የሴቱን አናቅም፣
ወንድ አንድ ሰው ሞተ።

አባቴን ወንድሜን፣
ልጄን ቢገሉብኝ፣
ነበር መናደዴ፤
ባሌን ቢገሉብኝ፣
ነበር መናደዴ፤
ጨከኑ በራሴ፣
ይቅር አለ ሆዴ።

ማረክን እንዳይሉ፣
ሰው የለ በጃቸው፤
ገደልን እንዳይሉ፣
ሞተው አገኟቸው።

ምን ይሉ እንግሊዞች፣
ሲገቡ አገራቸው?
ለወሬ አይመቹ፣
ተንኮለኞች ናቸው።

12/06/2026

ጠጅም አያምረኝ፣ ድሮ ጠጥቼዋለሁ፤
ስጋም አያምረኝ፣ ቋንጣ ሰይዬ በልቻለሁ፤
ቢርበኝ ከወንድሜ፣ ከአባቴ እበላለሁ።

ሺህ ብረት በግራው፣ ሺህ ብረት በቀኙ፤
ሺህ ፈረስ ከኋላው፣ ሺህ ፈረስ ከፊቱ፤
ይህን ሳታይ ሞተች፣ ኮሶ ሻጭ እናቱ።

አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቷችሁ፣
አቃጥሎ ለብልብ ፈጅቶ ይግደላችሁ።

ይህንን ሲሰማ ያጓራል አመሉ፤
ማናት ቢላችሁ፣ ምንትዋብ ናት በሉ።

12/06/2026

ሳላውቀው ሳላቅፈው፣
ሳልስመው ያለፈ ዘመኔ፤
ወዳጄ፣ የልቤ ሰው፣
ልጅነት ብቻ ነው።

አሁን ሳስታውሰው፣
ናፍቆት ሆነህ ቀረህ!

የልጅነት ናፍቆት! 💔

በፍቃደ አዘዘ

11/06/2026

ከህል ውሃ ሌላ፣
የሰው መኖር ትርጉም፣
የሰው መኖር መላ፣
አንድም ለካ በትዝታ፣
በትዝታና በተስፋ!

በፍቃደ አዘዘ..✍️

10/06/2026

"ዘመም ይላል እንጂ"

እንደ ጊዜው መክፋት
እንደ ግፉ መስፋት
እንዳገሩ ክስመት
እንዳገሬው ጥመት
እንደሰው ጭካኔ፥እንደ ልቡ ፍሬ
ታምር ነው መትረፍሽ፥ ታምር ነው መኖሬ::

የበጎ ሰው ሀሳብ፥ ሲካድ እለት በእለት
ጉድጓድ ተምሶለት፥ ሰብእና ሲቀበር
በዚህ ዓለም መኖር፥አያስመኝም ነበር ::

ምድሩ ሳር ቅጠሉ፥ በስጋት ተሞልቶ
የማለዳው ሰማይ፥ እንዳንቀልባ ቀልቶ
ታረደ
ነደደ
ከዘብጥያ ወጥቶ
ዘብጥያ ወረደ
የሚል ዜና ብቻ ፥ አየሩን ሲሞላው
ሰው በገዛ ጥላው ፥
በርግጎ ሲሸበር
በዚህ ምድር መኖር፥ አያስመኝም ነበር ፤

አዎ
ለጊዜውም ቢሆን ግፍ ያደነዝዛል
በደል ያስተክዛል
ጊዜም ጠብን ሽሮ፥ ወደ ፊት ይጓዛል
በልብ ሰሌዳ ላይ፤ ቂም ይደበዝዛል
በነገ ያመነ
ልጁን ቀብሮ መጥቶ ፥ ሚስቱን ያስረግዛል ::

ይቅርታና ምህረት
ፍቅርና ህብረት
ከግፍ ጋር ፍልሚያቸው፥ ቢሆን የሞት ሽረት
ዳገት ይወጣሉ፥ በንጥፍጣፊ አቅም
የመኖር ፍላጎት
ዘመም ይላል እንጂ ፥ተገርስሶ አይወድቅም።

(በዕዉቀቱ ስዩም✍️

10/06/2026

"ጨረቃ"

ሚስጥረኛ ወዳጅ፣
የሌሊት ጓደኛ፣
በጨለማ መካከል፣
የምትፈነጥቂ ብርሃን።

ምንም ብናገርሽ፣
የምትጠብቂው ሚስጥር፣
ለልቤ መሸሸጊያ፣
ለሐሳቤ ማረፊያ ነሽ።

ሰው ሲናፍቅ፣
ልብ ሲከብድ፣
ዝም ብለሽ ሰምተሽ፣
ተስፋን የምትሰጪ።

ሩቅ ብትሆኚም፣
ቅርብ የምትመስዪ፣
በሰማይ ላይ ሆነሽ፣
ልቦችን የምታበሪ።

አንቺ ነሽ ለኔ፣
የልቤ ጓደኛዬ፣
በዝምታ የምታዳምጪኝ፣
በብርሃንሽ የምታጽናኚኝ። 🌙

Cc የኛ ነገር Yegna N***r.

10/06/2026

"ሱሰኛ ሆኛለሁ"

ሱሰኛ ሆኛለሁ፣
ግን የአደንዛዥ አይደለም፤
የፍቅርሽ ሽታ፣
የፈገግታሽ ብርሃን፣
ልቤን ያለፍቃዱ እሄው ታስሬያለው።

ሱሰኛ ሆኛለሁ፣
ድምፅሽን ለመስማት፣
መልክሽን ለማየት፣
ስምሽን ለመጥራት፤
ቀንም ሆነ ሌሊት
ልቤ ይናፍቃል።

አንድ ቀን ባላይሽ፣
ዓለም ባዶ ይመስለኛል፤
አንድ ቃል ባልሰማ፣
ደስታዬ ይጎድላል።

ሱሰኛ ሆኛለሁ፣
የልብሽ ደግነት፣
የዓይንሽ ሙቀት፣
ከውበትሽ ባለፈ
ደግነትሽ በዝቶ፣
የዘወትር ፍላጎቴና
መድኃኒቴ ሆኗል።

ከዚህ ሱስ መፈወስ
ምንም አያሻኝም፤
ምክንያቱም ሕመሙ ፍቅር ነው፣
መዳኔን ከፈለሽ፣
ፈውሱም አንቺ ነሽ።

Cc የኛ ነገር Yegna N***r.

Address

Afar
Addis Ababa

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when የኛ ነገር Yegna Neger. posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share