03/09/2026
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ በምዕራብ ዓባያ ወረዳ ያይቄ ቀበሌ እያስገነባ ያለው የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤት ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ገለጸ
ዲላ ነሐሴ 28/2018 ዓ.ም
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ በምዕራብ ዓባያ ወረዳ ያይቄ ቀበሌ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በክረምት በጎ ፈቃድ እያስገነባ ያለው የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤት ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንደሚጠናቀቅ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርት ቢሮ ም/ኃላፊ ዶ/ር ብርሃኑ ገቦ ገልጿል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ብርሃኑ ገቦ እንደገለጹት፣ የ2018 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በአራት ዋና ዋና የሥራ መስኮች እየተከናወነ ይገኛል።
እነዚህም ሰው ተኮር ተግባራት፣ የመንገድ ደህንነት፣ መሠረተ ልማት እና ችግኝ ተከላ ሲሆኑ፣ በሰው ተኮር ተግባራት የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት ግንባታ፣ የማዕድ ማጋራትና የትምህርት ቤት ቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገ እንዳለ ተናግሯል።
በመንገድ ደህንነት ዘርፍ የእግረኞች መሻገሪያ ዜብራ መቀባት፣ የተሽከርካሪዎች ቴክኒክ ፍተሻ ማከናወን፣ የትራፊክ ሕግና የመንገድ አጠቃቀም ግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ በማለት ገልጿል።
በመሠረተ ልማት ዘርፍም የመንገድና የድልድይ ጥገና ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፣ በአካባቢ ጥበቃና በዘላቂ ልማት ላይ ያተኮረ የችግኝ ተከላም በተጨማሪ እየተከናወነ መሆኑን ተገልጿል።
በያይቄ ቀበሌ እየተገነባ ያለው የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤት ግንባታም አሁን ወደ መጠናቀቂያ ደረጃ ደርሷል። ለቤቱ የተሟላ የቤት ዕቃ ከማሟላት በተጨማሪ ሶስት ፍየሎች የሚሰጡ ሲሆን፣ በቤቱ ዙሪያ ለምግብነት የሚውሉ ሀለኮ፣ ማንጎና አቮካዶ ችግኞችም ተተክለዋል።
ይህም የበጎ ፈቃድ ተግባሩ መኖሪያ ቤት ብቻ በመገንባት የማይወሰን ሆኖ፣ ቤተሰቡ በቀጣይ ዘላቂ የኑሮ መሠረት እንዲኖረው የሚያግዙ ተጨማሪ ድጋፎችንም ያካተተ መሆኑን ተናግሯል።
የቤቱ ግንባታ በቀጣይ ሳምንት ተጠናቆ በክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት እንደሚመረቅ ተገልጿል።