11/06/2026
በብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የምርጫው አፈጻፀምና የድህረ ምርጫ ሥራዎችን ከነገ ጀምሮ በቀበሌ ደረጃ ይገመግማል
በብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አፈጻፀምና የድህረ ምርጫ ሥራዎች ግምገማ ከነገ ጀምሮ በቀበሌ ደረጃ ማካሄድ ይጀምራል።
የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ የ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የፓርቲው አፈፃፀምና የድህረ ምርጫ ስራዎችን በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ ጌቱ በመግለጫቸውም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝባችን ከሌሊት እስከ ሌሊት በመሰለፍ ድምፁን በመስጠት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ነው
በዚህም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ሰላማዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ በማካሄድ ኢትዮጵያውያን በፅናት አዲስ ታሪክ ጽፈዋል ብለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ አመራርና አባላት የምርጫ ስነ ምግባርን በማክበር ጉልህ ሚና መወጣታቸውን ነው የገለፁት።
ብልፅግና ፓርቲ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ መንትያ ግቦችን አስቀምጦ ፣ የምርጫ ቦርድን ህጎች ፣ አዋጅና መመሪያዎች ተከትሎ ፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በትብብር እና በፉክክር በመንቀሳቀስ ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ ለምርጫው ሰላማዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የሚያስችሉ ስራዎች በቁርጠኝነት ሲሰራ መቆየቱን አብራርተዋል።
ከቅድመ ምርጫ እስከ ምርጫው እለት የታየውን የአመራሮቻችንና የአባላችን የላቀ መናበብ፣ መቀናጀትና ቁርጠኝነት ግለቱን ጠብቆ ማስቀጠል እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የድህረ ምርጫ ሥራዎችን በስኬት በመፈፀምም የተጀመረውን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የብልጽግና ጉዞ ይበልጥ ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ አመራሮችን ጨምሮ በሁሉም ወረዳ የሚገኙ የብልፅግና ህብረት አመራሮች በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የተያዙ መንትያ ግቦችን ለማሳካት የተከናወኑ ስራዎችን በመገምገም በቀጣይ ተግባራት ላይ ተግባቦት መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
ከነገ ጀምሮም በክልሉ በሚገኙ በሁሉም ቀበሌዎች የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አፈጻፀምና የድህረ ምርጫ ስራዎች እንደሚገመገሙ ጠቁመው በግምገማው ላይም በክልሉ በገጠር እና በከተማ የሚገኙ የፓርቲው አባላት እንደሚሳተፉ ነው የገለፁት።
በመድረኩ ላይም ፓርቲው በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እቅዱ መሠረት በቅድመ ምርጫና በምርጫው ወቅት የነበረውን አፈጻጸም በመገምገም ጠንካራና ደካማ አፈጻጸሞችን እንደሚለዩ አብራርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ''በድህረ ምርጫ ወቅትም ትኩረት በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል''።
ስለሆነም በሚካሄደው ግምገማ በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው አባላት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አስተላልፈዋል።