11/10/2025
በኢትዮጵያ ታሪክ ስነዳ ሂደት ሞጋቹ ፕሮፌሰር አርፈዋል
ላ ጲ ሶ ጌ ታ ሁ ን ድ ሌ ቦ (ዶ/ር)
ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌታሁን ድሌቦ በቀድሞው በከንባታና ሐዲያ አውራጃ በኩፋላ ሐበሌ ግንቦት 12 ቀን 1930 ዓ.ም ተወልደው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በቢቾ ሆሣዕና ሚሽን ት/ቤትና በመንግሥት ትምህርት ቤት ሲከታተሉ ቆይተው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዳማ በሚገኘው በአጼ ገላውዴዎስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ባይብል አካዳሚ ተምረዋል፡፡
ከዚያም ወደ አሜሪካ በማቅናት በኮሙኒቲ ኮሌጅ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለው በኀብረተሰብ ታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። ከሐዋርድ ዩኒቨርሲቲም በአፍሪካ ታሪክ ጥናት የማስትሬት ዲግሪያቸውን፣ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካና በአውሮፖ ታሪክና በፍልስፍና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ ወስደዋል።
ዶክትሬታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ተሰጥቷቸው ለሁለት ዓመታት በቨርጂኒያ ዩንየን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሲያስተመሩ ቆይተው አብዮቱ ሲፈነዳ ‘የታሪክ አካል መሆን አለብኝ’ በማለት ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። ያኔ የነበራቸውን ስሜት ሲገልፁ “የኢትዮጵያ አንድነትን እንደ ጣኦት እያመለኩት መጣሁ” ይላሉ፡፡
ወደሀገራቸውም ተመልሰው በዚሁ ስሜትና ሀሳብ ዙሪያም ምርምራቸውንና ማስተማሩን ገፍተውበት አገራቸውን ያገለገሉ ምሁር ናቸው፡፡
በአሜሪካን ሀገር በፍልስፍና እና በታሪክ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ሲማሩ ከአምስት መቶ ተማሪዎች አንደኛ በመውጣት ከፍተኛ አድናቆት ማትረፍ ችለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ የአሜሪካን ሀገር ዩንቨርስቲዎች የነፃ የትምህርት ዕድል በአማራጭነት አቅርበውላቸዋል።
ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌታሁን ድሌቦ ብዙ በተማሩበት ዘርፍ ባደረጉት ምርምር በርካታ የታሪክ መፃህፍትን ያሳተሙ ሲሆን ዐበይት በሆኑ ሀገራዊ የታሪክ ክስተቶችም ላይ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ማለትም በሬዲዮና በቴለቪዥን ላይ በመቅረብ ጠለቅ ያለ ትንተና በመስጠት ይታወቃሉ ፡፡
ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌታሁን ድሌቦ ካሳተሟቸውም የታሪክ ስራዎች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡-
1. የኢትዮጵያ የገባር ሥርዓትና ጅምር ካፒታሊዝም፣ 1ኛና 2ኛ የታሪክ መጻሕፍት
2. የኢትዮጵያ ረጅም የሕዝብና የመንግሥት ታሪክ 1ኛ መጽሐፍ፣
3. የኢትዮጵያዊነት ታሪካዊ መሰረቶችና መሳሪያዎች(ታሪክ)
4. የቀይ ባሕርና የዓባይ ሸለቆ ሚና፣ የምፅዋ ሲምፖሲየም-1974
5. የኢትዮጵያ የመከራ ሥርዓትና የኤርትራ ጥያቄ፣ 1ኛ፣2ኛ እና 3ኛ መጽሐፍ
6. አጭር የጌዴኦ ህዝብ ታሪክ ከ1982-1966
7. የምርትና የባህል ዘመቻ በከንባታና ሀዲያ አውራጃ
8. የአዲስ አበባ መዲና እድገትና ሚና በኢትዮጵያ ታሪክ
9. ናሽናል አትላስ እና
10. ሌሎች በርካታ የታሪክ መጻሕፍት አሳትመው ለአንባብያን አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት የራሳቸው ፍልስፍና (school of thought) እንዳለቸውም የሚነገርላቸው ፕሮፌሰሩ፣ በዚህም አስተምህሯቸው ምክንያት ብዙ ፈታናዎችን እና ተቃውሞችን ማስተናገዳቸውን በተለያዩ ጊዚያት ከሰጡት ቃለ መጠይቆች ተደምጠዋል፡፡
በባህሪያቸው ግልፅ፣ ታማኝ እና ሰው አክባሪ እንደሆኑ በባልደረቦቻቸው የሚመሰከርላቸው ፕሮፌሰር ላጲሶ “ሰው ሁሉ አንድ ነው፤ ከአንድ ዘር ነው የመጣው፤ ሰውን ከሰው የሚለየው ስራው ነው” ይላሉ፡፡
በአንዳንድ የምርምር ስራዎች ላይ ፈጥነው ወደ ድምዳሜ የሚደርሱ እና ስሜታዊነትንም የሚያንፀባርቁ ሃሳቦችን አካተዋል በሚል ትችት ሲሰነዘርባቸው ይስተዋላል።
“የኢትዮጵያ ታሪክ የሁሉ ካልሆነ የማንም አይሆንም” የሚል መርህ እንዳለቸው የሚናገሩት ፕሮፌሰር ላጲሶ፣ የአንዱን ብሔር ወይም ሐይማኖት ታሪክ ነጥለን ከዚያ አንፃር ብቻ የኢትዮጵያን ታሪክ የምንጽፍ እና የምንተነትን ከሆነ ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ታሪክ ማወቅ እንደማይቻል ይናገራሉ፡፡
“የኢትዮጵያ ታሪክ የክርስትናው፣ የእስልምናው እና የሌሎች ሃይማኖቶች እንዲሁም የብዙ ቋንቋዎች እና ህዝቦች መስተጋብር ነው” በሚል ሙግታቸው ይታወቃሉ፡፡
ባለትዳር እና የሦስት ሴት ልጆች አባት የነበሩት የ87 አመቱ የእድሜ ባለፀጋ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ላጲሶ ድሌቦ ባደረባቸው ህመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። የእርሳቸው ለኢትዮጵያ ታሪክ ስነዳ ያደረጉት ምርምርና አበርክቶ ግን ለትውልዱ ትልቅ ቅርስ ሆኖ የሚዘልቅ አሻራ ነው።
ምንጭ ፡-
• ታሪካዊ መዝገበ ሰብ (ጌታሁን እንግዳ)
• የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ለሚሊኒየም ያሳተመው አጀንዳ
• ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ጋር ያደረጓቸው ቃለ ምልልሶች
Yahode ያሆዴ Hadiya