የኛ ነገር Yegna Neger.

የኛ ነገር Yegna Neger. ትዝታ ለሕይወት ሥር ሲሆን፣
ተስፋ ወደፊት የሚያራምደን ኃይል ነው።

11/08/2026

በቀደም ደወለች

በቀደም ደወለች፣
አወጋች፤ አወጋሁ፤
እስከመጨረሻ
“ደህና ሰንብቺ” ብዬ፣
የስልኬን አፍ ዘጋሁ።

ከዚያም ቀናት አለፉ፣
ወራት እንደ ቅጠል
እግሬ ሥር ረገፉ።
ልጅ ሆና የማውቃት፣
እናቷን አከለች፤
ዘጠኝ ወር አርግዛ፣
ሞት ተገላገለች።

ምን አሸዋ ቢያልቡ፣
ስፋስ ቢያጋልቡ፣
ደመናውን ጠርበው፣
ሀውልት ቢያሰገነቡ፤
“ሞትና ክስመት ነው
የተፈጥሮ ግቡ”
ብዬ እንዳልፅናና፣
በሟቷ ፊት ለፊት፣
ሀሳብ ሁሉ መና፣
ምክር ሁሉ ወና።

እንባን አይገድብም፣
የሰው ፍልስፍና።
በፍራሻችን ሥር፣
ቃሬዛ ተጣብቆ፤
በልብሳችን ገበር፣
ከፈን ተደብቆ፤
የእድሩ ጥሩንባ፣
ከሙዚቃው ልቆ፤
በዘንድሮ ጣቶች፣
ከርሞ ላይነካ።

“ደህና ሰንብቺ” ማለት ዘበት ኖሯል ለካ!

09/08/2026

ነጋ ደሞ ጎህ ቀደደ!

29/07/2026

ለናፈቃቹ!

መንገድ ምንጣፍ ቢሆን፣
ህብረ ቀለም ያለው፤
ታዛዥ እንደ እኔ ልብ፣
ገራም እንደ አንቺ ልብ።

መንገድ ምንጣፍ ቢሆን፣
ቢጠቀለል ቢያጥር፤
ሳልሄድ፣ ሳትመጪ፣
እንገናኝ ነበር።

ያኔ ነበር
ፍቅር ትርጉም የሚያገኘው፤
ከንቱ መናፈቅን፣
ጊዜንና ቦታን
በአንዴ ስንገድላቸው።

መንገድ ምንጣፍ ቢሆን፣
ቢጠቀለል ቢያጥር፤
ፍቅርሽ ተጠቅልሎ፣
አንቺም ተጠቅልለሽ፤
እኔም ተጠቅልዬ፣
አስረሽኝ፣ አስሬሽ።

ቦታ ቦታ ጠቦት፣
ጊዜ ሁሉ ቆሞ፤
ናፍቆት ባለቀሰ፣
ሜዳ ላይ ተጋድሞ።

28/07/2026

ህይወት ሳውቃት...

ጣዕም ነበራት፤ ምሬትም፤
ውሃ ነበረች፤ እሳትም።
ደስ ስትልም፣ ስትከፋም፣
ለዛዋ ከጉያዋ አይጠፋም።

እለያት ነበር፣
በአቋቋሟ፣
በአረማመዷ።

ህይወት ሳውቃት...

በልጅነት፣
ሳቅ ነበራት፤
ጣፋጭ እንባም።

ሰው ነበራት...
ማን ሰበራት?

ህይወት...
ምን ነካት?
ምን ሰነከላት?
ማን መተንፈስ አሳከላት?

"ሞቴን አየሁ በሕልሜ።"መንቀሳቀስ አልችልም፤ መናገርም አልችልም። ከሰው ጓሮ ወድቄ፣ በጥልቅ ጨለማ ውስጥ ለቀናት ተጋድሜ እቀራለሁ።በመጀመሪያው ቀን ነፍሴ ልትነሳ ፈለገች፤ ግን አልቻለችም። ...
27/07/2026

"ሞቴን አየሁ በሕልሜ።"

መንቀሳቀስ አልችልም፤ መናገርም አልችልም። ከሰው ጓሮ ወድቄ፣ በጥልቅ ጨለማ ውስጥ ለቀናት ተጋድሜ እቀራለሁ።

በመጀመሪያው ቀን ነፍሴ ልትነሳ ፈለገች፤ ግን አልቻለችም። ድብልቅልቅ ያለ ድምፅ እሰማለሁ፤ መናገር እፈልጋለሁ፣ ግን ድምፅ አይወጣም።

"አነሳለሁ" ማለት እፈልጋለሁ፤ ነገር ግን "ሞቻለሁ" የሚል እውነት ፊቴን ይመታኛል። ልቤ አይቀበለውም፤ ግን እውነታው አይቀየርም።

በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ማንም የማያየኝ፣ የማላውቀው አውሬ በዙሪያዬ ሲያንዣብብ እሰማለሁ። አይኔ አይከፈትም፤ አንገቴ አትቀናም። "ሂድ... ሂድ..." የሚል ድምፅ ከውስጤ ይገፋፋኛል፤ እኔ ግን ምንም ማድረግ አልችልም።

ቀናት አለፉ። በሦስተኛው ቀን ሰውን ማየት ብቻ ሳይሆን፣ የእናቴን ድምፅ መስማት ምኞቴ ሆነ። መጮህ ፈለግሁ፤ ግን ድምፅ አልወጣም። በዚያ ቀን ሰውነቴ እንደከዳኝ ተሰማኝ።

አንድ ምሽት የጎረቤት ድምፅ ጆሮዬን ነካ። በቀረው ኃይሌ "እዚህ ነኝ... ከጓሮ ጀርባ..." ለማለት ሞከርሁ፤ ግን የወጣው ድምፅ ለእኔም እንኳ አልተሰማኝም።

ተስፋ ቀስ በቀስ ጠፋ። ከዚያ በኋላ ስለ ሕይወት ሳይሆን ስለ መቀበር ማሰብ ጀመርሁ። ከአያቴ ጎን ብቀበር ብዬ ተመኘሁ፤ ያ ምኞት ብቻ ፈገግታን አመጣልኝ።

ከግማሽ ሌሊት በኋላ አንድ እውነተኛ ድምፅ ሰማሁ። ግን ያኔ በጣም ዘግይተው ነበር። ነፍሴ ወጥታ ነበር። ሊያድኑኝ አልቻሉም፤ ግን የሚያውቁኝ ዘመዶቼ አስከሬኔን አገኙት።

በዚያ ጊዜ አንድ ምኞት ብቻ ቀረልኝ፤ እናቴን ማግኘት። ማቀፍ ባልችልም፣ ማናገር ባልችልም፣ ቢያንስ አስከሬኔ እሷ ዘንድ ይድረስ ብዬ ፈጣሪን ለመንሁ።

እርሱም ምኞቴን አልነፈገኝም።

እየተሸከሙ ወደ እናቴ አደረሱኝ። አይኖቼ ማየት ባይችሉም፣ ጠረኗን አሸተትሁ፤ ድምጿንም ሰማሁ።

ያን ጊዜ የተሰማኝን ደስታ በቃላት መግለጽ አልችልም። እንባዬ ገደብ አላወቀም፤ እንደ ሕፃን ልጅ አለቀስሁ።

እሷም "ልጄ... ልጄ..." እያለች አቀፈችኝ። በስሜ እየጠራች፣ "አይ ልጄ... እንዴት እንዲህ ሆንክ?" ብላ አለቀሰች።

የእንባዬን መልስ እንደተረዳች፣ "አይዞህ... አይዞህ..." እያለች አጽናናችኝ።

እኔም የመጨረሻ ኃይሌን ሰብስቤ ቀስ ብዬ እንዲህ አልኳት፦

"እናቴ... ከአያቴ ጎን እንድቀበር አድርጊልኝ።"

ቃሉን ከተናገርኩ በኋላ የምመኘው ነገር አልቀረም። የሞት ፍርሃትም ሆነ የሕይወት ምኞት በአንድ ላይ ጸጥ አሉ።

በዚያ ቅጽበት አንድ እውነት ብቻ ገባኝ፤

ሰው በመጨረሻ የሚፈልገው ሀብት ወይም ዝና አይደለም፤ የሚወደው ሰው እቅፍ ነው።

ከእናቴ እቅፍ ውስጥ ያለውን ሙቀት እየተሰማኝ፣ እንባዬ ቀስ በቀስ ረገበ፤ ሕልሙም በጨለማ ውስጥ ቀስ ብሎ ተሟሟ።

💔💔

ሐምሌ, 20, 2018, @ 12:10 ስዓት

09/07/2026

ማነው ሚፈልገኝ፣
በማይነጋ ሌሊት፣
በማይመሽ ቀን መሀል፣
ተዘርሬ ስገኝ?

ከተውሽኝ ወዲህ፣
እርቃኗን ቀረች ነፍሴ፤
ከሰው አውድ ተነጥዬ፣
ተለየሁ ከራሴ።

ተመልሼ ልምጣ፣
ለመመለስሽ ነይ፤
ምሶሶዬን ልጥል፣
ማይገርሽን ጣይ።

አዲስ ቤት መገንባት፣
ዛሬ መች ይበጃል?
ለምዶ ወደተወው፣
መመለስ ይቀላል።

ሐሳብ አልክልሽ፣
ቁና ጤፍ ሰፍሬ፤
ባዶ እጄን አልቆምም፣
ከደጅሽ ደፍሬ።

ፅንፍ የለሽ ይቅርታ፣
ውሰጅ ከከንፈሬ።

07/07/2026

ክህደት!

ክህደት ጩኸት የለውም፣
በዝምታ ይገድላል፤
በፈገግታ ተሸፍኖ፣
ልብን ቀስ ብሎ ያፈርሳል።

እምነት እንደ ብርጭቆ ነው፤
ከተሰበረ ይሰነጠቃል፤
ቢለጠፍም እንኳን፣
የስብራቱ አሻራ ይቀራል።

የቀረበ እጅ ሲጎዳ፣
ሕመሙ ይበልጥ ይከብዳል፤
ጠላት ቢወጋህ አይገርምም፣
ወዳጅ ሲክድ ግን ያቃጥላል።

ክህደት መጨረሻ አይደለም፤
የእውነት መጀመሪያ ነው።
የጣለህን ተወው፣
የቀረልህን አክብር፤
ልብህን በቂም ሳይሆን፣
በጥበብና በይቅርታ ያዘው።

28/06/2026

የሞትኩ ለት!

ጊዜ የማይሽረው ጠባሳ
ጥሎብኝ የልብ ቁስል፤

አይ ሰው ማስመሰሉ
ከንፈሩ ይቀርባል ያውቀኝ ይመስል።

እኔው ተሰብሬ ተመልሼ
ደግሞ እኔው ነኝ ተወቃሽ።

ነገሩማ ገዳዬ ነው
ለቀብሬ ዋና አልቃሽ።

የውሃ ጠብታ ለጥሜ ያልሰጠኝ
ስኖር እስከ ዛሬ፤
ወይን ያድላል ለተስካሬ።

ማን ነበር ራበኝ ስለው
ከርሱ ከፍሎ ለኔ የሚሰጥ?

ብቻ ልሙት አይገደውም
የዚያን እለት ጮማ መቁረጥ።

ልብሴ አድፎ ተቀዳዶ
መቼ ያኔ አይተውኛል?
ብቻ ልሙት እንጂ
ነጭ በነጭ ያለብሱኛል።

አሁን አሁን ትንሽ ሰው ነኝ
በየትም ያለው፤
ብቻ ልሙት ያከብሩኛል።

ይህ ከንቱ ዓለም
እንዳየሁት በገባኝ መጠን እስከማውቀው፤
በሕይወት ሳለሁ ውዱ ነገር
የሞትኩ ለት ከውሸት ጋር ርካሽ ነው።

23/06/2026

ሳላውቀው ሳላቅፈው፣
ሳልስመው ያለፈ ዘመኔ፤
ወዳጄ፣ የልቤ ሰው፣
ልጅነት ብቻ ነው።

የልጅነት ናፍቆት!💔

19/06/2026

‘ቀይ መስመር’

ቀይ መስመር አለ፣
በልቤ ላይ የተሳለ፤
ከትዝታሽ የተነሳ፣
በትዝታ የተጻፈ።

ልረሳሽ ብዬ ስሄድ፣
መንገዴን ቢበዛ ርቀት፤
ከስምሽ ጋር እተናነቃለሁ፣
ያ የፍቅር ህመም እየነደፈኝ።

አልፌው ልሂድ ብል እንኳ፣
እግሬ ወደ ኋላ ይመለሳል፤
የነበረውን ደስታ እያሰብኩ፣
በውስጤ ናፍቆት ይነሳል።

ቀይ መስመር አለ፣
ማንም የማያየው ግን ያለ፤
በፍቅር የተሳለ ቁስል፣
ከዘመን ጋር የማይጠፋ።

ምልክት ሆኖ የቀረ፣
በሁሉም ልብ የሚኖር፤
በቀይ የተሳለ ማይታይ ድንበር።

Address

Addis Abeba
Addis Ababa

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when የኛ ነገር Yegna Neger. posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Shortcuts

Share