24/05/2026
በዛሬው ዕለት ግንቦት 15/2018ዓ.ም. ራሱን የ«አፋር ነፃነት ግንባር» ብሎ የሚጠራው ሀይል አባላትን ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ የሚረደው የትጥቅ መፍታት፣ ከወታደራዊ አገልግሎት ማሰናበትና መልሶ ማቋቋም (DDR) መርሃ-ግብር ማስጀመሪያ ፕሮግራም በጎሊና ወረዳ በይፋ ተካሂዷል።
የመድረኩን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱ ሙሳ እንደገለጹት፤ ይህ ቀን በክልላችን ዘላቂ ሰላምን፣ መረጋጋትንና ልማትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ላለው ጥረት ትልቅ ማሳያና ታሪካዊ ቀን ነው ብሏል። ሰላም ወዳድነትን በተግባር ላሳዩት የሀይሉን አመራር እና አባላት አመስግኖ ሌሎች ሀይሎች ከነዝህ ሀይል በመማር በሰላም ወደ ማህበረሰባቸው መቀላቀል አለባቸው፤ መንግስታችን ሁልጊዜም ለሰላም ቁርጠኛ ነው በማለት ገልጿል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የብሔራዊ መልሶ ማቋቋም ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ይህ የDDR ሂደት መጀመር በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የሰላምና የደህንነት ግንባታ ስራ ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ጠቁመው፣ የግንባሩ አባላት ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው በልማት ላይ እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በዚህ ታላቅ መድረክ ላይ፦
የብሔራዊ መልሶ ማቋቋም ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፣
የአፋር ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና አመራሮች፣
የዞን አራትና የወረዳው አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝቷል።
ቁጥራቸው 300 የሚጠጉ የዚሁ ግንባር አባላት የተሳተፉበት ይህ የDDR መርሃ-ግብር፤ አካባቢያችንን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግና ህዝባችን በጋራ ወደ ልማት ፊቱን እንዲያዞር ለሚደረገው ጉዞ ትልቅ በር ከፋች ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ሰላም ለክልላችን፣ ልማት ለህዝባችን!