22/07/2025
ትኩረት ለምርጫውና 15ቱ ነጥቦች
🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴
አሕመዲን ጀበል
💥💥💥💥💥
ትኩረታችሁን ምርጫው ላይ አድርጉ። ምርጫ ሲባል ቁልፍ ነገሩ «ይሆኑናል» የሚባሉ ሰዎችን በሁሉም እርከን የማስመረጥ ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያ ምርጫዬ እገሌ ነው ብሎ በመጻፍ ብቻ እዉን አይሆንም። ታች መርዶ ከመስጂድ ጀምሮ ዉይይትና ዝግጅት ማድረግን ይጠይቃል።
ምርጫ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የብዙሃን ዉጤት ነው። ስለሆነም ዉይይትና ምክክር ይሻል። ይህ ደግሞ «እኔ እገሌን መርጣለሁ» ብሎ ተቀምጦ በግለሰብ ደረጃ ከመጠባበቅ ይልቅ በየመስጂዱ «በየዘርፉ ማንን ብንመርጥ ይሻላል?» ብሎ በጋራ መምከርና መዘጋጀት ይፈልጋል ማለት ነው።
ስለሆነም በየሰፈራችንና መስጂዳችን መመካከር ይገባናል። ለዚህ ያግዝ ዘንድ ከዚህ በፊት በተለያዩ መድረኮች ካነሳኋቸው ችግሮች ባሻገር ጥቂት ተጨማሪ ነጥቦችን ለማከል ዉደድኩ። መልካም ንባብ!
ከባለፉት አስርት ዓመታት ሕዝበ ሙስሊሙን ካስቆጡና የቅሬታ ምንጭ በመሆን ለትግል ያነሳሱትን የመጅሊስ ችግሮችን በሚገባ ማስታወስና መረዳት ይገባናል።ይህ ደግሞ ወሳኝ የሚሆነው ከድምጻችን ይሰማ የዓመታት ትግል በኋላ በሕዝበ ሙስሊሙ ቀጥተኛ ተሳታፊነት የሚደረግ የመጀመሪያው ምርጫ እንደመሆኑ ሕዝበ ሙስሊሙ በተለይ ደግሞ የድምጻችን ይሰማ ትውልድ ከባለፉት ችግሮችና ስህተቶች በመማር የመራጭነት ሚናችንን በአግባቡ መወጣት ይገባዋል። ምክንያቱም ለትግልና ዋጋ መክፈል ያበቃውን መጅሊስ ሚናውን ባለመወጣቱ ከፌደራል እስከ ወረዳ ባሉት በየትኛውም እርከን እንዳይደገም መጠንቀቅ ብልህነት ነውና።
ያሳለፍንበትን የዘመናት የመጅሊስ ችግሮችን በሚገባ መረዳትና ማስታወስ መቻል የምንመርጣቸውን ሰዎችን ከዚያ አንጻር መገምገም እንድንችል በእጅጉ ያግዘናል። ከዚህ በታች የተጠቀሱት እንደ የአከባቢው ሁኔታ መጠነኛ ልዩነት ሊኖርበት አልያም ሌላ ተጨማሪ የሚጠቀሱ ነጥቦችም ይኖራሉ።በዚህ ረገድ በየአከባቢያነችን በትክክል የሚወክሉንን ተመራጮች ለመለየትና ለመምረጥ የምናደርጋቸውን ዉይይቶች ያግዝ ዘንድ የሚከተሉትን 15 ነጥቦችን በአብነትነት መጥቀስ ጠቃሚ ይሆናል።
1) የመጅሊስ አመራሮች የሕጋዊነታቸውና የቅቡልነታቸው ምንጭ ሕዝበ ሙስሊሙ ሳይሆን መንግስት በመሆኑ ተማኝነታቸው ሕዝበ ሙስሊሙ ሳይሆን ለመንግስት እንዲሆን በማድረግ የመጅሊስ አመራሮች የሕዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች መሆን አለመቻል።
2) ወደ መጅሊስ የሚመጡት አካላት ዓላማቸው ሕዝበ ሙስሊሙን ከልብ ለማገልገል ሳይሆን ከመጅሊስ መገልገልና መጠቀም ላይ ትኩረት ያደረገ መሆን።
3) በተለያዩ እርከኖች በመጅሊስ ዉስጥ ተቀጣሪ ሆነው በመግባት ዘወትር ከመጅሊስ የማይጠፉ በመጅሊስ የመንግስት አምባሳደር በመሆን የመንግስት ጆሮ ጠቢ፥ ለመጅሊስ አመራሮች አቅጣጫና ትዕዛዝ ሰጪ በመሆን የሚያገለግሉ ስዉር እጆች መኖር።በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የመጅሊስ ፕሬዝዳንት የነበሩት የሐጅ አብዱራህማን ሙዳ ጉዳይ ነው። ሐጅ አብዱራህማን ሙዳ አላህ ይማራቸውና በፕሬዝዳንትነታቸው ዘመን በ1990ዎቹ አጋማሽ በዚህ መልኩ በተቀጣሪ ስም የተሾመባቸው ግለሰብ መኖሩን ተረዱ። ደፈር ብለውም ያንን በሠራተኛ ስም በስዉር የተሾመባቸውን ግለሰብ ከሥራ አገዱ። ይህን እርምጃ በመውሰዳቸው በማግስቱ እርሳቸው ራሳቸው ከመጅሊስ መሪነት ታገዱ። በዚያው የመጅሊስ የስልጣን ዘመናቸው አበቃ።
4) መጅሊስ ሕዝበ ሙስሊሙን ቢያስተባብርና ቢያንቀሳቅስ የሚኖረውን አቅም ባለመገንዘብ በእጁ ምንም አቅም እንደሌለው ራሱንና ተቋሙን አሳንሶ የማየት ችግር።ከዚህ የተነሳ አመራሮቹ ትኩረት በሕዝባቸው ዘንድ ክብርና ሞገስን ከማግኘት ይልቅ ፍላጎታቸው ከመንግስት ሰዎች ጋር ጥሩ ትስስርን መፍጠር ያደርጉታል።
5) ሌላኛው ደግሞ መጅሊስ ለምን እንደሚያስፈልግና እንደቆመ ያለመረዳት ችግር ነው።ይህም የመጅሊስን ራዕይ፥ ተልዕኮ፥ ግቦች፥ ዓላማዎች፥ እሴቶች፥ ስትራቴጂዎች፥ ተግባራትን፥ የሥራ ክፍሎችን፥ መተዳደሪያ ደንቦችን ያለማወቅን ጭምር ያካትታል።
6) መጅሊስ የየትኛውም ጀመዓ ወይም ቡድን የግል ንብረት ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሙስሊም የጋራ ተቋም መሆኑን አምኖ ያለመቀበል እና ይህን ታሳቢ ያለማድረግ ችግር ነው።
7) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች እና የኢትዮጵያ ዑለማ ምክር ቤት ማለትም የመጅሊስ አስተዳደርና የዑለማ ዘርፉ ሚናና ተግባር ግልጽ ያለመሆን ችግር። በተደጋጋሚ እንደታየው የመጅሊስ አመራሮች ጠንካራ የዑለማ ምክር ቤት እንዳይኖር በማድረግ ከዚህ በፊት ተጠሪነቱ ለፕሬዝዳንቱ፥ ሌላ ጊዜ ለጠቅላላ ጉባኤው በማድረግ የመጅሊስ አመራሩ በምግባሩ ምክንያት ተግዳሮት ሲገጥመው የህዝብ ቁጥና ቅሬታ ማብረጃ መሣሪያ በማድረግ በመኖርና ባለመኖር መካከል ግልጽ ያልሆነ ሚና እንዲኖረው መደረጉ።
8) መጅሊስን የአገልግሎት መስጫ ማዕክል ሳይሆን የቡድን ፥ የጀመዓና የመዝሀብ ዉክልና ማስጠበቂያ መሆንና ከርሱ ስብስብ ዉጭ ያሉት አካላት ወደ መጅሊስ እንዳይገቡ፥ ያልገቡት ደግሞ የሚዳከሙበትን መንገድ በመፈለግና በነርሱ ጉዳይ በመጠመዳቸው ለማህበረሰቡ ቁም ነገር የሚሰሩበት ጊዜና ሀሳብ ማጣት።
9) መንግስት መጅሊስን ይመለከተው የነበረው ሕዝበ ሙስሊሙን የሚወክልና የሚያገለግል የሙስሊሞች ተቋም ሳይሆን የህዝበ ሙስሊሙን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠርበት፥ ከሙስሊሞች መካከል የማይፈልጋቸውን አካላት እንቅስቃሴን የሚያግድበት፥ መግለጫ በማውጣት የሚያቀግዝበት የራሱ የደህንነት መስሪያ ቤት ቅርንጫፍ አድርጎ ከመመልከቱ የሚመነጭ ችግሮች።
10) የመጅሊስ ዓመታዊ እቅዶች፥የአፈጻጸምና የኦዲት ሪፖርቶች ለሕዝበ ሙስሊሙ ይፋ ያለመሆን ሕዝበ ሙስሊሙም የራሱን መጅሊስ የሚቆጣጠርበት ስርዓትና አካሄድ ያለመኖር ችግሮች።
11) የተጠያቂነት ችግሮች ሌላኛው ነው። መጅሊስ በታሪኩ በርካታ ምዝገበራዎች፥ ስርቆት፥ ማጭበርበሮችኑና ግልጽ የጥቅም ትስስር ያስተናገደ ተቋም ቢሆንም እስከ ዛሬ ድረስ በታሪኩ አንድም ግለሰብ ለጥፋቱ ተጠያቂ አልሆነም። ይህ ደግሞ የትኛውም የመጅሊስ አካል የሆነ ሰው በተጠያቂነት ስሜት እንዳይሰራ በር በመክፈት ተቋሙ የተዝረከረከ እንዲሆን አድርጓል።
12) ቀላል ቁጥር የሌላቸው የመጅሊስ ተቀጣሪ ሠራተኞች ወደ መጅሊስ የመጡበት፥እድገት የሚያገኙበት ወይም በዚያ የሚቆዩበት ሁኔታ በብቃት ሳይሆን በታማኝነት፥ በጀመዓ ወገንተኝነት፥ በብሄር ፥በዝምድናና በጥቅም ተጋሪነት መስፈርት መሆኑ ሌላኛው ምክንያት ነው።
እያንዳንዱ የመጅሊስ መሪ ወደ ስልጣን ሲመጣ «የኔ» የሚላቸውን ሰዎችን ወደ ተቋሙ በማምጣቱና እርሱ ሲለቅ እነዚያ ሠራተኞች የማይለቁ በመሆናቸው መጅሊስ በተለያዩ ዘመን ወደመጅሊስ በመጡ «የኔዎች» የተሞላ ተቋም እንዲሆን አድርጓታል። ይህ ደግሞ ከአመራሮቹ ባሻገር ተቀጣሪ ሠራተኞችም ተቋሙ ለቆመለት ተልዕኮ አጋዥ ሳይሆን መሰናክል እንዲሆኑ አድርጓል።
13) ከዚህ በፊት በተለያዩ እርከኖች ላይ በመጅሊስ አመራርነት የመጡ አካላት የራሳቸው ቋሚ ሥራና የገቢ ምንጭ የሌላቸው በመሆኑ መጅሊስ ለነርሱ የአግልግሎት ሥፍራ ሳይሆን የመገልገያ ስፍራ እንዲሆን አድርጓል። ከመጅሊስ ከወጡ ለኑሯቸው መውደቂያ ስለሌላቸው የመጅሊስን ስልጣን ላለመልቀቅ እንዲዋደቁ አድርጓቸዋል።
14) የመጅሊስ ሌላ ችግር የተቋሙ ብቸኛ የገቢ ምንጭ ሐጅ መሆኑ ነው።ከዚህ የተነሳ የመጅሊስ እንደተቋምም ሆነ እንደሠራተኛ ዓመታዊ እቅዳቸው ዋንኛው ማዕከል ሐጅ ነው። አመራሮችም ሆኑ ተመራጮች ጠቀም ያለውን ዓመታዊ ገቢያቸውን የሚያገኙት ከሐጅ አገልግሎት በመሆኑ ሁሉም በየፊናው በሐጅ አገልግሎት ሂደት ላይ ቀጣተኛ ሚና ቢኖራቸውም ባይኖራቸውም የገቢ ምንጫቸውን ለማጎልበት በሐጅ ተግባራት ላይ ለመሳተፍ ይጥራሉ። በዚህም እንደየአቅማቸው ከአበል እስከ ኮሚሺን ለማግኘት ይጥራሉ።
ከዚህ አሰራር የተነሳ የሐጅ አገልግሎት ለመጅሊስ ከዓመታዊ ተግባራቱ መካካል የሚጠቀስና ወደ ግማሽ የሚጠጋውን ጊዜውን እስከ መውሰድ የሚደርስ ሆኗል።ተቋሙ በሐጅ ጉዳይ ዉስጥ ሰምጦ በመግባት ሌሎች የሥራ ክፍሎቹ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዳይወጡ አድርጓል።
15) በተቋሙ ዉስጥ የጉልበተኞች ጎልቶ መውጣት ሌላኛው ቁልፍ ችግር ነው። የመጅሊስ የሥራ አስፈጻሚዎች የተቋሙ ከፍተኛ አመራር በመሆን በጋራ የመሪነት ሚና መስጠት ቢገባቸውም አንዳንድ የሥራ አስፈጻሚዎች በተለየ መልኩ ከመንግስት ጋር በሚኖራቸው ልዩ ቁርኝት በተቋሙ አካሄድ ላይ የጎላ ተሰሚነትና ወሳኝነት መኖር ሌላኛው ችግር ነው።
ይህን ሚና የሚወጡት የመጅሊስ ጸሐፊው፥ ምክትል ፕሬዝዳንቱ፥ ሌላ ጊዜ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ አንዳንዴም የጽ/ቤት ሐላፊው የመሆንበት ጊዜም ተስተውሏል። ከዚህ የተነሳ በሥጋት ነጻ ለመሆን፥ ጥቅምን ለማስከበርና በመጅሊስ ለመቆየት አዋጭ ስልቱ እንደ የሥራ አስፈጻሚ አንዳች ዉሳኔ ለመወሰን ያ ከመንግስት ጋር ልዩ ቁርኝነት ያለው ግለሰብ የሚይዘውን አቋም እያዩ የራስን አቋም ከርሱ አቋም ጋር እያስተካከለ መኖር ይሆናል።
እነዚህንና ሌሎች ነጥቦችን እያነሳን በግልጽ በመወያየት ካለፉት ስህተቶች በመማርና ስህተቶቹ እንዳይደገሙ ለማድረግ እንድንችል ተገቢ የሆኑ ሰዎችን ለሁሉም የመጅሊስ እርከን አመራሮች ለመምረጥ እንዘጋጅ። አበቃሁ።